የቦረና ሳይንት ወረሂመኑ ብሔራዊ ፓርክ ከሐይቅ ከተማ 226 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከምትገኘው የቦረና ወረዳ ዋና ከተማ መካነ ሰላም ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ 22 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ቦታው የመንግሥት የተፈጥሮ ደን ተብሎ የተያዘው በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1952 ዓ/ም ነበር፡፡ በፓርኩ ውስጥ በርካታ የዱር እንስሳት ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን ለአብነትም ቀይ ቀበሮ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ የምኒልክ ድኩላ ይጠቀሳሉ፡፡ በርካታ የአዕዋፍ እና ዕጽዋት ዝርያዎችም በፓርኩ ይገኛሉ፡፡

በረባዳው አካባቢ እስከ ዓባይ ሸለቆ የሚደርሰው ጥቅጥቅ ደን ሲገኝ፤ በውርጫማው አካባቢ ደግሞ የጓሣ ቦታ አለው፡፡ ሌላኛው የፓርኩ ገጽታ በተራራማ አካባቢ እስከ አማራ ሳይንት ወረዳ ድረስ የሚገባው የጓሳ ምድር ነው፡፡ የጓሳው ክፍል ውርጫማ የአየር ንብረት ያለበት በመሆኑ በአብዛኛው የተሸፈነው ለቤትና ለግጦሽ በሚያገለግል የጓሳ ሣርና የደጋ ጽድ ዝርያዎች ሲሆኑ፣ አየር ንብረቱ የሚስማማቸው የዱር እንስሳትና አዕዋፍም በብዛት ይኖሩበታል፡፡ ቦረና ሳይንት ወረሂመኑ ብሔራዊ ፓርክ ለጎብኝዎች መረጃ የሚሰጥ ማዕከል እና ጽ/ቤት ያለው ሲሆን በዛ ያሉ ጎብኝዎችንም በማስተናገድ ላይ ይገኛል፡፡
Was this helpful?