መቅደላ ከሐይቅ ከተማ 140 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከምትገኘው የተንታ ከተማ ሰሜን ምስራብ አቅጣጫ 17 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ታሪካዊ አምባ ነው፡፡ የመቅደላ አምባ ዙሪያ ገባውን ከርቀት ለመቆጣጠር የሚያስችል በመሆኑና በዘመኑ ስትራጂያዊ ሥፍራ ላይ በመገኘቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ጥቅም ነበረው፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስም ይህን ጠቀሜታ በመረዳት የወሎን ዘመቻ መቅደላን በመያዝ ሲያጠናቅቁ አስከ ሞት ከቦታው ጋር ያስተሣሠራቸውን ታሪክ ፈጽመውበታል፡፡ በዚህም መቅደላ ሲነሣ ዐፄ ቴዎድሮስ መታወሳቸው የማይቀር ጉዳይ ሁኗል፡፡

ዐፄ ቴዎድሮስ መድፎችን እና የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን በጋፋት ካሠሩ በኋላ መቀመጫቸውን ከደብረ ታቦር ወደ መቅደላ ያዞሩት የአምባው መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ማራኪ ከመሆኑ በተጨማሪ ራስን ከጠላት ለመከላከል ሁነኛ ስፍራ በመሆኑ ነበር፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ አንድ መግቢያ በር ብቻ ባለው አምባ በሠሩት ግምጃ ቤት ሴባስቶፖልን ጨምሮ ሌሎች 15 መድፎች፣ 11,063 የተለያዩ ጠመንጃዎች፣ 875 ሽጉጦች፣ 481 ሳንጃዎች፣ 555 የመድፍና የሞርታር አረሮች እንዲሁም 83,563 የተለያዩ ጥይቶች አሰባስበው እንደነበር በታሪክ ተመዝግቧል፡፡


መቅደላ አምባ የታላቁን ንጉሠ ነገሥት የአንድነት፣ የሥልጣኔ እና ሥርዓት የማበጀት ሕልም እና አሳዛኝ ፍጻሜ በዓይነ ኅሊና እያሰቡ የሚጎበኙት መዳረሻ ነው፡፡ በአምባው ላይ ከሚገኙ የታሪክ ዐሻራዎች እና በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአብርሃ ወጽበሃ መንግሥት መመሥረቷ ከሚታመነው የመቅደላ ማርያም በተጨማሪ በዙሪያው በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአብርሃ ወአጽብሐ ዘመነ መንግሥት መተከሉ የሚነገርለት የሰላምጌ ሥላሴ፣ በዐፄ ላሊበላ ዘመን ከአንድ ዐለት ተፈልፍሎ የተሠራው የፋላ አምባ ጊዮርጊስ እና በንጉሥ ሚካኤል ዘመነ የተሠራው ተንታ ሚካኤል የመሳሰሉ ሊጎበኙ የሚገባቸው ቦታዎች ይገኛሉ፡ እንግዶች እስከ መቅደላ አምባ ድረስ በመኪና መሄድ የሚችሉ ሲሆን በአምባው በተሰራው ሎጅም የምግብ፣ መጠጥና መኝታ አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ፡፡
Was this helpful?