ግሼን ደብረ ከርቤ ከሐይቅ ከተማ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ 112 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኝ ልዩ አምባ በ517 ዓ.ም በአባ ፈቃደ ክርስቶስ በተሰኙ አባት የተመሠረተች ታሪካዊና አንጋፋ የሃይማኖት ቦታ ናት፡፡ የግሼን አምባ የመጀመሪያ መጠሪያ ደብረ ነጎድጓድ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ቅዱስ ላሊበላ ወደ ግሼን መጥተው በአምባው ቤተ ክርስቲያን ለመፈልፈል እንዳሰቡ በሚነገርበት ዘመን ደግሞ የግሼን መጠሪያ ወደ ደብረ እግዚአብሔር ተቀይሯል፡፡

ብዙም ሳይቆይ በንጉሥ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት ድጋሚ ስሟ ተቀይሯል፡፡ በዘመኑ አምባው ከእምነት ቦታነቱ በተጨማሪ የአስተዳደር ቦታ በመሆን የነገሥታት ልጆች እንዲማሩና በዚያው እንዲኖሩ በመደረጉ አምባው ደብረ ነገሥት በመባል ተጠራ፡፡ አምባው የነገሥታት ልጆች መኖሪያ መሆኑንን ለማመልከት የተሰጠ ስያሜ ነበር፡፡

ግሼን ደብረ ከርቤ የሚለውን ስያሜ ያገኘችው በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉን ከሲናር ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት በዚህ አምባ ሲያሳርፉ ቦታው ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል መገኛ ነው በማለት “ደብረ ከርቤ” ብለው ሰየሙት፡፡ ይሄ ስያሜም ዘመናትን በመሻገር አሁን ድረስ በመጠሪያነት ያገለግላል፡፡

እግዚአብሔር አብ         ቅ/ማርያም             ሙዚየም

በግሸን አምባ በዋጋ የማይገመቱ ውድ ቅርሶችን የያዘ ሙዚየም፣ የእግዚአብሔር አብ፣ የቅድስት ማርያም፣ የቅዱስ ሚካኤል፣ የቅዱስ ገብርኤል እና የቅዱስ ኡራኤል አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡ በሙዚየሙ የነገሥታት ስጦታዎች፣ የብራና መጻሕፍት፣ መስቀሎች እና የተለያዩ ቅርሶች ለዕይታ ቀርበዋል፡፡ በግሼን ከሚገኙ በርካታ የብራና መጻሕፍት መካከል አያሌ የሐገር ውስጥና የዓለም ታሪክን የያዘው መጽሐፈ ጤፉት ተጠቃሽ ነው፡፡ የመጀመሪያው የግእዝ ተአምረ ማርያም ቅጂም የሚገኘው እዚሁ ነው፡፡

Was this helpful?

Traveler Testimonials

Share your experience to help other travelers plan their visit.

Add Your Testimonial

Your email address will not be published. Required fields are marked *