የአድዋ ድል በተለይ ከደቡብ ወሎ ዞን ጋር የጎላ ትስስር አለው፡፡ የዚህ ታላቅ ጦርነት ሰበብ ተደርጎ የሚወሰደው ባለ 20 አንቀጽ የውጫሌ ውል ሚያዝያ 25 ቀን 1881 ዓ.ም በዳግማዊ አፄ ምኒልክና በኢጣሊያው ተወካይ ኮንት አንቶሎኒ መካከል የተፈረመው በአምባሰል ወረዳ ውጫሌ ከተማ 15 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ‹‹ይስማ ንጉስ ›› በተሰኘው ታሪካዊ የቱሪዝም መዳረሻ ሲሆን፤ የሰላም ድርድር የማይሳካ ሆኖ ጦርነቱ ግድ በሆነበት ጊዜ በወርሃ መስከረም በ1888 ዓ.ም ዳግማዊ አፄ ምኒልክና አማካሪዎቹ የጦርነቱን አዋጅ ያረቀቁት በወረኢሉ ወረዳ ደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር ደጀ ሰላም ካለው ፎቅ ነው፡፡ በመቀጠል አዋጁ የጥቅምት እኩሌታ ከሁሉም የሀገሪቱ ግዛት ወረኢሉ እንዲከትና ወደ አድዋ እንዲዘምት አዋጅ የተነገረበትና ትጥቅና ስንቅ የተዘጋጀበት፤ እውነትን ይዘው ለሀገራቸው በክብር ለመሞት የቆረጡት በእምነታቸው ጭምር በሃይማኖት አባቶች ታግዘው በጾምና ጸሎት ሲዘምቱ የወረኢሉ ደብረ ሰላም ቅ/ጊዮርጊስ ደብር ጽላት አብሮ እንደዘመተና በድል እንደተመለሰ ይነገራል፡፡ በተጨማሪም ንጉስ ሚካኤል በርካታ የጦር ሰራዊት ይዘው ከንጉሱና ከሌሎች የሀገራችን ክፍል ከመጣ ዘማች ጋር በመሆን ተዋግተው ለድል በቅተዋል፡፡ በአጠቃላይ ደቡብ ወሎ ከዚህ ታላቅ የድል በዓል ጋር አብረው የሚነሱ ዋና ዋና ታሪካዊ የቱሪዝም ሀብቶች በስፋት የሚገኙበት ሲሆን በዓሉን በዚህ ዞን ማክበር ለየት ያደርገዋል፡፡
Was this helpful?