የደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በ1220 ዓ/ም በንጉሥ ነአኩቶ ለአብ ዘመን በወረኢሉ የተመሠረተ ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያን በ15ኛው ክፍለ ዘመን በጦርነት በመውደሙ ቤተ መንግሥታቸውን ወረኢሉ አካባቢ ድርማ በሚባል ቦታ የመሠረቱት ዐፄ ገላውዴዎስ በየዋሻው ተደብቀው ከጥፋት የተረፉትን ንዋየ ቅዱሳት በማሰባሰብ በመጠነኛ የሣር ቤት እንደገና አሠርተውታል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ በዐፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥትም ለሦስተኛ ጊዜ የተሠራ ሲሆን አሁን ያለው ቅርጽ እና መጠሪያ ስም የያዘው ከዐድዋ ድል በኋላ በዳግማዊ ምኒልክ በልዩ ሁኔታ በመሠራቱ ነው፡፡ የዐድዋ ጦርነት ሲነሣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት አብሮ መዝመት እና ተራዳኢነት ለዘመናት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ይወሳል፡፡ የወረኢሉ የሃይማኖት አባቶች ዳግማዊ ምኒልክ ሠራዊታቸውን በወረኢሉ አሰባስበው ወደ ዐድዋ ሲዘምቱ ይዘውት የዘመቱት ጽላት የወረኢሉ ደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስን መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ለ15 ቀናት በወረኢሉ ከሰነበቱ በኋላ በጊዮርጊስ ዕለት በቤተ ክርስቲያኑ ሥርዓተ ቅዳሴ አጠናቀው “የወረኢሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦትን” ይዘው ወደ ዐድዋ ዘምተዋል፡

ዳግማዊ ምኒልክ ከዐድዋ በድል አድራጊነት ሲመለሱም ይዘውት ለዘመቱት ለሰማዕቱ ጊዮርጊስ ክብር ሲሉ ቤተ ክርስቲያኑን ልዩ በሆነ ሁኔታ ለማሠራት ልጃቸውን ንግሥት ዘውዲቱን በበላይነት እና ራስ ሀብተ ማርያምን በእንደራሴነት ወክለዋል፡፡ በዚህ ጊዜም ንጉሠ ነገሥቱ ታቦቱ “ጠላትን አዋርዶ ድል አጎናጽፎ በሰላም እንድመለስና ሀገሬንም ሰላም ያደረገ ታቦት በመሆኑ ስሙን ደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ብየ ሰይሜዋለሁ” በማለታቸው ከዚያን ዘመን ጀምሮ ደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ተብሎ በመጠራት ላይ ይገኛል፡፡
ደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በልዩ ጥበብ በሐረግ በተጌጡ እንጨቶች የተሠሩ 3 ትልልቅ በሮች፣ 30 መስኮቶች፣ ጣሪያውን እና ግድግዳውን የሚያገናኙ ልዩ ቅርጽ ያላቸው 30 ዓምዶችና ሠረገላዎች የተሠራ ክብ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ዐፄ ምኒልክ ቤተ ክርስቲያኑን ማራኪ በሆነ መንገድ ከማሠራታቸው በተጨማሪ የራሳቸውን እና የቤተሰቦቻቸውን የራስ ወርቅ፣ ካባዎች፣ የተለያዩ መስቀሎች፣ የብራና መጻሕፍትና ሌሎች ውድ የሆኑ አልባሳትን እና ንዋየ ቅዱሳትን በስጦታ አበርክተዋል፡፡
በዚሁ ቤተክርስቲያን የሚገኘው ሌላው ታካዊ ነገር የራስ ሀብተ ማርያም የመቃብር ቦታን የያዘው ሕንጻ ነው፡፡ ሕንጻውን ራሳቸው ራስ ሀብተ ማርያም ያሠሩት ሲሆን ግድግዳው እና ጣራው በቅርጽ ከተሠሩ ጥርብ ድንጋዮች የተገነባ ነው፡፡ ከውጫዊው የሕንጻው ግድግዳ ድንጋይ ላይ በወረኢሉ ያለውን የክርስትና እና እስልምና ሃይማኖቶች ወዳጅነት ለማሳየት የጨረቃ እና የመስቀል ቅርጽ ያለው ዓርማ ተደርበታል፡፡ ዓርማው ከአንድ ድንጋይ ላይ ተቀርጾ የተሠራ ሲሆን በተለያዩ የሕንጻው ክፍሎች ይገኛል፡፡ መስቀሉ ክርስትናን ጨረቃው ደግሞ እስልምና ሃይማኖቶችን እንደሚወክሉ አባቶች ያስረዳሉ፡፡

ራስ ሀብተ ማርያም የንግሥት ዘውዲቱ የእናታቸው ወንድም ሲሆኑ ከዓድዋ ድል መልስ የወረኢሉ ደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሲሠራ በዳግማዊ ምኒልክ ትዕዛዝ ለንግሥት ዘውዲቱ እንደራሴ ሁነው የተመደቡ ሰው ናቸው፡፡ የወረኢሉ ተወላጅ የሆኑት ራስ ሀብተ ማርያም ከንግሥቲቱ ጋር በመሆን ቤተ ክርስቲያኑ ዳግማዊ ምኒልክ በአዘዙት መሠረት በማሠራት እና የውስጡ ግድግዳ በመንፈሳዊ ስዕሎች እንዲዋብ ግንባር ቀደም ሚና መጫወታቸውን ታሪክ ይመሰክራል፡፡
Was this helpful?