ለታሪካዊው የዓድዋ ጦርነት መነሻ በመሆን የሚጠቀሰው የውጫሌ ውል በንጉሥ ምኒልክ እና በጣልያን ንጉሥ ወኪል ኮንቲ አንቶሎኒ መካከል አምባሰል አካባቢ ውጫሌ በሚባል ቦታ ሚያዚያ 25 ቀን 1881 ዓ.ም የተደረገ የውል ስምምነት ነው፡፡ በአንቀጽ 3 እና 17 ምክንያት በተነሣ አለመግባባት የውጫሌ ውሉ እንዲፈርስ ከፍተኛ ትግል ያደረጉት እቴጌ ጣይቱ ነበሩ፡፡ በወቅቱ “እኔ ሴት ነኝ፣ ጦርነት አልወድም፡፡ ግን እንዲህ መሳዩን ውል ከምቀበል ጦርነት እመርጣለሁ፡፡ ይስሙ ንጉሥ!” የሚል ታሪካዊ ንግግር አድርገዋል፡፡ ይኼን ንግግራቸውን ተከትሎም የውጫሌ ውል የተጻፈበት ቦታ “ይስማ ንጉሥ” በሚል ተሰይሞ እዚህ ዘመን ደርሷል፡፡

የይስማ ንጉሥ መታሰቢያ ሙዚየም የዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ መታሰቢያ ሐውልት
ይስማ ንጉሥ ከደሴ በወልዲያ መንገድ 6ዐ ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከምትገኘው ውጫሌ ከተማ ለመድረስ 7 ኪ.ሜ ሲቀር ከዋናው መንገድ 4 ኪ.ሜ ወደግራ ገባ ብሎ ከአምባሰል ተራራ ግርጌ የሚገኝ ታሪካዊ ቦታ ነው፡፡ በአሁን ጊዜ የዘመኑን ታሪካዊ ሁነቶችን የሚዘግቡ ቅርሶችን በማሰባሰብ የይስማ ንጉሥ ሙዚየም የተገነባ ሲሆን ለዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱም በቦታው የመታሰቢያ ሐውልት ቁሞላቸዋል፡፡
Was this helpful?